Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የብአዴን መክዳትና የ“በቀል” ፍርሃት የወለደው “የኢኮኖሚ አብዮት” በኦሮሚያ

በህወሃት ገደብ የለሽ የሥልጣን ፍቅርና የቁስ ሰቀቀን ውልቅልቋ እየወጣ ያለችው ኢትዮጵያ ከፍታው ርቋት የቁልቁለቱን ጉዞ ተያይዛዋለች። ለወጣበት ዘውግ ልዕልና የሚተጋው ህወሃት ህግና ሞራል በማይዳኘው ድርጅታዊ ቀኖናው እየተመራ ኢትዮጵያን ማድማቱን ቀጥሎበታል።

እስር፣ ቶርቸር፣ ስቃይ፣ ስደት፣ ሞትና የግዞት ኑሮ ከህወሃት ዘውግ ጥላ ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እድል ፈንታ ሆኗል። ከነዚህ በመከራ ከሚዳክረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል አንዱ የኦሮሞ ሕዝብ ነው። እውነታው ግን ሰፊና ለም የሆነ መሬት ላይ የሰፈረው የኦሮሞ ሕዝብ በቁመቱ ልክ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ ሊከበርለት እንዳልቻለ ወራሪው ህወሃት ራሱ ለፖለቲካ ፍጆታም ቢሆን ያመነውና ማንም ሊከደው የማይችል የአደባባይ ሃቅ ነው።

በአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ላይ የአንበሳውን ድርሻ ሊይዝ የሚገባው የኦሮሞ ህዝብ በህወሃት እንደ ጭቃ ተላቁጦ፣ ተድቦልቡሎ ተጠፍጥፎ በተሰራው ኦህዴድ እንዲወከል የተደረገው የኦሮሞ ሕዝብ፣ ዝሆን ሆኖ ሳለ ለጥንቸል ከሚሰግደው ኦህዴድ ለሚምልበት ህዝብ ያተረፈው በአደባባይ መረሸን፣ በሥነ-ልቦና ረገድ ሽባ በሚያደርገው የማዕከላዊ ቶርች መዳረግና ለአሳፋሪ ረሃብና ድህነት መጋለጥን ብቻ ነው። አብዛኞች እንደሚስማሙበት ኦህዴድ ከዚህ የተሻገረ በጎ ድርጅታዊ ታሪክ የለውም። ታሪክ አለው ብለው እድሜ የሚቆጥሩ ቢኖሩ አመራሮቹ ከሰውነት ደረጃ ወረደው የሸክላነት ዘመናቸውን ከማስላት የሚዘል አይሆንም።

ከላይ እንደተባለው እንደ ጭቃ ተጠፍጥፎ ወገኖቹን እያስረሸነ 27 የባርነትና የአሽከርነት ዓመታትን ያሳለፈው ኦህዴድ “ምራው” የተባለውን ሕዝብ በሚመጥን መልኩ ፖለቲካዊ ቁመና ቀርቶ የጥሩ ዕድር ሽታ የለውም። በዚሁ መለኪያ ኦህዴድ የፖለቲካ አቅሙ የተሽመደመደ ቢሆንም፣ ከነሙሉ ጀሌው እንዲዘርፍ ግን ፈቃድ ተሰጥቶታል። ወይም ለስልት ሲባል “እንዲበሰብስ” ተደርጓል። ከጅምሩ ከምርኮኞች መካከል አቅማቸው ለአሽከርነት ይመጥናል የተባሉት ተመርጠው የፖለቲካ ድርጅት ታቤላ የተሰጣቸው “አመራሮች” የኦሮሞን ህዝብ በተመለከተ የተሰጣቸውን የቤት ስራ እንዲወጡ በመሆኑ ይህንን ሃላፊነታቸውን ሲወጡ ኢኮኖሚውን እንዲበዘበዙ፣ ህዝቡንም አዘርፈው ተራፊውን እንዲለቃቅሙ ተፈቅዶላቸዋል።

ኦህዴድ ሲጠፈጠፍ ቀዳሚ የነበሩት ስሜት አንጋሽ “ፖለቲከኞች” የፖለቲካ ጉልበታቸውን የሚፈትሹትም ዘርፈው ባካበቱት ሃብት አይነኬነት የሆነው በዚሁ መነሻ ይሆናል ። ከመልማዮቹ በወሰደው ትምህርት ሁለተኛው የኦህዴድ ትውልድም ቢሆን ከተላላኪነት ሚናው በተጨማሪ “ዲጂታል” ኢኮኖሚያዊ በዝባዥነት መለያ ባህሪው ሆኗል። ለዚም ነው ኦህዴድ ሲናድ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ “ሌቦች” ተብለው የዘብጥያ ደረሰኝ በማንኛውም ጊዜ እንደሚቆረጥባቸው ተነግሮ ዲዳ ሆነው እንዲቀመጡ፣ አለያም እስር ፍርሃቻ በጓሮ ለተሻሻለ አሽከርነት ማመልከቻ እንዲያስገቡ የተመቻቹት።

የህወሃት አመራሮች ኦሮሚያ ላይ በዘረጉት የጫት እና የቡና ንግድ ዱባይ ላይ የገበያ አዳራሽ ሲገነቡ፤ የኦህዴድ አመራሮች የክልሉን ዓመታዊ በጀት እያራቆቱ አዲስ አበባ ላይ በዘመድ አዝማድ ሥም ቪላ ቤቶች መስራታቸውን እንደስኬት ይቆጥሩታል። የህወሃቱ ኤፈርት ግዙፍ የንግድ ኢምፓየር የ“ኢትዮጵያ” የሚባለውን እየዋጠ፣ አህጉር አቋራጭ የንግድ ግንኙነት ሲዘረጋ፤ የኦህዴዱ ቱምሳ ኢንዶውምውንት በኦሮሚያ ብድርና ተቋም በኩል “እየመራሁት ነው” የሚለውን ህዝብ ወገብ በሚጎምድ የብድር ወለድ ቁም ስቅሉን ያሳያል። ቱምሳ “ብድርና ቁጠባ”፣ “ጅምላ ንግድ”፣ “የእርሻ ስራ” (ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ . . . ምርት)፣ የአረም መድሃኒት፣ ከስሮ የተንገዳገደ የትራንስፖርት ዘርፍ፣ የላስቲክ ጫማ ንግድ፣ ላይ ተተክሎ ሲባትት፤ ኤፈርት እነሱን እየዘረፈ ከማዕድን እስከ ቤቶች ግንባታ፣ ከሜካናይዝድ እርሻ እስከ ኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ ከማህበራዊ አገልግሎት እስከ ሆቴልና ቱሪዝም፣ ከኮንስትራክሽን እስከ ትራንስፖርት ዘርፍ፣ ከኤሌክትሮኒክ ሚዲያ እስከ ህትመት ፣ . . . ለቁጥር በሚታክቱ የንግድ መስኮች ተሰማርቶ  እየገደለና ቶርቸር እያደረገ ለያዘው ዘረኛ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ የበላይነት ተግቶ ይሰራል። በራሱ ክልል ማዳበሪያ እንኳን መሸጥ የተከለከለው ኦህዴድ ከዚህ በላይ አሳፋሪና የገለማ ታሪክ አይመዘገብለትም። ልደቱም ይህንኑ የገለማበትን ዓመታት ከመቁጠር አያልፍም።

የማዕከላዊ፣ ቂሊንጦ፣ ቃሊቲና በአደባባይ የማይነገሩን እስር ቤቶች የሥራ ቋንቋ ኦሮምኛ እስኪመስል ድረስ የኦሮሞ ልጆች የእስር ቤቶች ቋሚ ቤተሰብ ሲሆኑ፤ በየጎዳናው ሲወድቁ መንገድ ጠራጊ የሆኑት የኦህዴድ አመራሮች የድርጅታቸውን ዕድሜ ከመቁጠር የተሻገረ ረብ ያለው የፖለቲካ ሚና በክልሉም ሆነ በኢትዮጵያ ደረጃ ማሳየት ያልቻሉት በዚሁ ተፈጥሯቸው ሳቢያ ነው።

ህወሃት የትግራይን ትምህርት ዕድገት ጉዞ በጥራት ደረጃ ሲለካው ኦህዴድ የኦሮሚያን ትምህርት በሽፋን ይገልፀዋል። መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ስለ ትግራይ ክልል ገበሬዎች ምርትና ምርታማነት ማሳደጊያ ዘዴዎች ወርክ ሾፕ ሲያዘጋጅ፤ አምቦ ዩኒቨርስቲ በክልሉ ስላለው “የሽብር ስጋትና ጠባብነት” “አውደ ጥናት” ያዘጋጃል። የአድዋ ከተማ ነዋሪዎች ከህወሃት አመራሮች ጋር ስለ ኢንዱስትሪ ልማት አስፈላጊነት ሲመክሩ፤ የኦህዴድ አመራሮች ምስራቅ ሐረርጌ ላይ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “ጠቀሜታ” ለህዝብ ይሰብካሉ። ትውልድ እንደ ከብት መኖ ሲመነዠክ፣ እነሱ ነገ አንቆ የሚይዛቸውን ትውልድ ዘንግተው ለከርስ የሚሆነውን ያግበሰብሳሉ።

ጥሬ ዕቃው ባሌ ፋብሪካው መቀሌ መሆኑ ግድ የማይሰጣቸው የኦህዴድ አመራሮች የህወሃትን አንጋሽነት ሚናቸውን ከመወጣት ጎን ለጎን ኦሮሚያን ዘርፎ ለዘራፊ የማመቻቸት ብቸኛ ተልዕኳቸውን በማስፈጸም እኩይ ድርጊት ተጠምደዋል። የዚህ ሁሉ ተደራራቢ በደል ውጤት የመሬት ባለቤትነትን መነሻ በማድረግ የታፈነው አመፅ በኦሮሚያ ሊቀሰቀስ ችሏል። ይህ ሲባል ግን ተቆርቋሪዎች የሉም ማለት ግን አይደለም። በአቋማቸው እስር የተፈረደባቸው፣ ደብዛቸው የጠፋ፣ ውስጥ ሆነው የሚሸረሽሩ ጊዜ የሚገልጻቸው ስለመኖራቸው ጥርጥር የለም። መረጃ ከማቀበል ጀምሮ!!

ከዝምታ ወደ አደባባይ ዓመጽ . . .

መነሻውን የመሬት ባለቤትነት (“የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን” በመቃወም) መደብ ተኮር አድርጎ ተቃውሞውን የጀመረው የኦሮሚያ አመፅ በሺህ የሚቆጠሩ ቄሮዎችን ገብሮ፣ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩትን ለአሰቃቂ እስር ዳርጐ፣ . . . እዚህ ደርሷል። የኢኮኖሚ የራስ-ገዥነት መልክ ይዞ የተነሳው ተቃውሞ የመደብ ጥያቄ ነበር ቢባልለት ከእውነታው መራቅ አይሆንም። የአመፁን ተራዛሚነት ተከትሎ የተቀነቀኑ የፖለቲካ ነፃነት ጥያቄዎች ግን የታፈነውን አመፅ ሥረ-ምክንያት በሚገባ የገለጸ ነበር።

ጥልቅ መገፋትና በደል አምጦ የወለደው የኦሮሚያ አመፅ የኦህዴድን የፖለቲካ መዋቅር በማፈራረስ ብቻ የተመለሰ አልነበረም። ይልቁንስ በክልሉ የነበሩ የገዥው ኃይል ማህበራዊ መሰረት የነበሩ ፋብሪካዎችንና ድርጅቶችን ከጥቅም ውጪ በማድረግ የቁጣውን ልክ አሳይቷል። ለአመፁ መቀልበስ ከውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች አኳያ ሊቀርቡ ከሚችሉ ምክንያቶች ውስጥ፤ የኦሮሞ ልጆች የባዶ እጅ ትግል (በብረት ያልተደገፈ መሆኑ) እና የህወሃት ህግና ሞራል የማይዳኘዉ ምህረት የለሽ የኃይል ፍጅት ተጠቃሽ ምክንያት ናቸው። በዚህ መነሻና ከተወሰደው ልምድ አንጻር ከዚህ በኋላ ለአመጽ የሚመጡ የኦሮሞ ልጆች ባዶ እጃቸውን ለተቃውሞ ይነሳሉ ብሎ መገመት የሚቻል አይመስልም።

ይህን መራርና የሚጠበቅ የበቀል ስሜት መገመት የማይከብዳቸዉ የህወሃት አመራሮች የኦሮሞ ወጣቶችን ልብ ለመማረክ ኦሮሚያ ላይ አዲስ ድርሰት ደርሰው በኦህዴድ በኩል ተውኔቱ  ከተጀመረ ሰነባብቷል። ይህን የፖለቲካ ቲያትር የኦሮሚያ “የኢኮኖሚ አብዮት” ሲሉ ይጠሩታል። በኦህዴድ ሰዎች ብዙ እየተባለለት ያለው የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት ደራሲና ቀማሪ ህወሃት ስለመሆኑ ክርክር የሚያነሱ የሉምና ዝርዝር አያስፈለገውም። አማራ ክልል የተነሳው ቀውስ ላይ ትኩረት ለማድረግ ኦሮሚያን “በደም ጉቦ” ለማስታገስ የታለመ ድርሰት መሆኑንን ግን መጠቆም አግባብ ይሆናል።

የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት ለጊዜው መነሻ አደረጋቸው የሚባሉ ዘርፎች፡- “ኦዳ የተቀናጀ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር” እና “ኬኛ ቤቬሬጅ (Kegna Beverage) የለስላሳ መጠጦች አክሲዮን ማህበር” ናቸው። የኢኮኖሚ አብዮቱ ለጊዜው ይፋ ያልተደረጉ የግብርና፣ የእንሰሳት ሀብት፣ የቡና ምርት፣ … ላይ እሴት ጨምሮ ወደ ውጪ መላክን ያካተተ ዕቅድ እንዳለው የኦህዴድ አመራሮች ሲደሰኩሩ ተሰምቷል። የኢኮኖሚ አብዮቱ በህዝቡ፣ በባለሃብቱና በክልሉ አስተዳደር የጋራ ቅንጅት እንደሚመራ አማላይ በሆነ መልኩ እየነገረ ይገኛል። የኢኮኖሚ አብዮቱ የህወሃትን የፖለቲካ የበላይነት ሥልጣን በማስቀጠል የህወሃት-ኢህዴድ ማህበራዊ መሰረቶችን ለይቶ የሚያበለጽግ መሆኑን ምክንያት እያጣቀሱ ከወዲሁ በድፍረት መናገር ይችላል።

አንደኛ፡- የኢኮኖሚ አብዮቱ በህዝቡ፣ በባለሃብቱና በክልሉ መንግሥት የጋራ ቅንጅት ተግባራዊ ይሆናል ቢባልም፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የዕቅዱ ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉት ኦህዴድና ድርጅታዊ የድጋፍ መሰረት ያላቸው የተለያዩ በፋይናንስና ባንክ ላይ የተሠማሩ እንዲሁም ሌሎች “የሕዝብ”ና የግል ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች ደግሞ “የህዝብ ባንክ”፣ “የህዝብ ድርጅት” በሚል ሥም የተቋቋሙ ንብረትነታቸዉ የኦህዴድ አመራሮች፣ በክልሉ ላይ በሚደርሰው በደል የማይሞቃቸው የማይበርዳቸው የክልሉ ባለሀብቶችና በአትሌትክሱ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ የአትሌቶች ከፍተኛ አክሲዮን ድርሻ ያላቸው የባንክና ፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች አትራፊ ድርጅቶች ናቸው።

ህዝቡ ባለበት ኑሮ ውድነት ጫና የተነሳ እና “መንግስት” ነኝ በሚለው ኃይል የሥልጣን ቆይታ ጊዜ ላይ ጥርጣሬ ያለው በመሆኑም በአክሲዮን ግዥ ላይ እጁን የሚሰድ አይመስልም። በመሆኑም የኢኮኖሚ አብዮቱ የኦህዴድና ድርጅታዊ የድጋፍ መሰረት ያላቸው የባንክ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖችና ሌሎች ድርጅቶች ባለሃብቶች በኩል በአደባባይ የሚፈፀም የንግድ ጋብቻ ይሆናል። ይህ ጋብቻ የክልሉን ሃብት በህጋዊነት ሥም ለመመዝበር በር ከመክፈት የተሻገረ ሚና አይኖረውም። ሁኔታው ህወሃት በማዕከላዊ አገዛዝ የያዘውን የበላይነት ከኃይል እመቃ ጎን ለጎን እንዲያጠናክር ዕድል ይፈጥርለታል። ኦህዴድም በሥሩ የተኮለኮሉ ጥገኛ ባለሃብቶችን ይዞ ለክልሉ ወጣቶች የማይጨበጥ ተስፋ እየጋተ የፈረሰ የፖለቲካ መዋቅሩን ለመጠገን ጊዜ ያገኝ ይሆናል። በመሰረቱ ኦህዴድ በክልሉ ዉስጥ አለኝ የሚለዉን ማህበራዊ መሰረት (አርሶ አደሩንና የከተማ አነስተኛ ዘርፍ ላይ የተሰማራዉን ሰራተኛ) እየካደ በክልሉ ዉስጥ ከጥገኛ ባለሃብቶች ጋር መሞዳሞድ የድርጅቱ መገለጫ ሆኗል። ለዚህም በክልሉ በታየዉ አመጽ ድርጅቱ “ማህበራዊ መሰረቶቼ ናቸዉ” የሚላቸዉ ኃይሎች ሳይቀሩ ተሳታፊ ሆነዋል። እነዚህን ኃይሎች ሲገፋ የኖረ ጥገኛ ድርጅት ዛሬ ላይ በህወሓት ባርኮት የኢኮኖሚ አብዮት አቀጣጥያለሁ ቢል ጉዳዩ የቃሉን ያህል ቀላል እንዳልሆነ መረዳት አንደማይከብድ ከወዲሁ አስተያየት እየተሰጠ ነው።

ሁለተኛ፡- በኦሮሚያ ክልል የተነሳው ህዝባዊ አመጽ የፖለቲካ ነፃነትን ያንጸባረቀ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ እንጂ የሥራአጥነት ጉዳይ ብቻ አይደለም። በአመጹ የፊት መስመር የታዩት ወጣቶች የማህበራዊ ፍትህ ጥያቄዎች በ“ኦዳ ትራንስፖርት አክሲዮን” አለያም በ“ኬኛ ቤቨሬጅ የለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ” መቋቋም የሚመለስ ሳይሆን፤ ኦሮሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አደባባይ ላይ በህዳጣኖች ከመመራት ተሻግሮ በቁመቱ ልክ ሲወከል የኦሮሞ ጥያቄያ እንደሚመለስ ከገባቸው ቆይቷል። አሁን በሚደሰኮረው የኢኮኖሚ አብዮት የሲቪክ መብቶችም ሆነ የፖለቲካ መብቶች እንዲሁም ማህበራዊ መብቶች ላይ ያሉ ተጽዕኖዎችና ቅሬታዎችን መመለስ እንደማይቻል ግልጽ ነው። የኦህዴድ ሰሞነኛ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ለዓመታት የተከማቸውን ህዝባዊ ጥያቄ ሊያዳፍነው አቅሙ የለውም።

ሦስተኛ፡- የመሬት ባለቤትነትን ጥያቄ አስታከው ከዝምታ ወደ አደባባይ አመጽ የተሻገሩት የኦሮሞ ልጆች ዛሬ ላይ ከህወሃት ጋር የማይሽር ደም ተቃብተዋል። በብዙሃኑ የኦሮሞ ቤት በግፍ ያልተገደለ፣ የአካል ጉዳተኛ ያልሆነ፣ ቶርቸር ሰውነቱን ያልበጣጠሰው፣ በአሰቃቂ እስርቤት ያልታሰረ፣ ተገፍቶ ያልተሰደደ የቤተሰብ አባል ፈልጎ ማጣት አይታሰብም። ኢሬቻ ላይ የወደቁ የኦሮሞ ወጣቶች (ሌሎችም እጅግ በርካታዎች አሉ) ብቻ ሳይሆኑ፤ የኦሮሞ ባህል ጭምርም ነው። እናት በልጇ አስከሬን ላይ ተቀምጣ እንድታለቅስ የተደረገችበት ሊረሳ የማይችል ፋሽስታዊ ድርጊት አይደለም በኦሮሞ ወጣቶች፤ ነፃነትን በተጠሙ ኢትዮጵያዊያን አዕምሮ ተቀርፆ የቀረ የመሪር ሃዘን ውርስ ነው። በብዙ መልኩ ከህወሃት ጋር ቂምና በደል የተቃባው ወጣቱ ክፍል እንኳንስ በማይጨበጥ ተስፋ፣ በሚታይና በሚጨበጥ ጥቅማጥቅም የሚደለል አይመስልም። በቅርቡ በህወሃት ባርኮት ተለቀቀ የተባለዉ “የወጣቶች ሥራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድ” ዉስጥ የኦሮሚያ ድርሻ 6.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ ከዚህ ብር ላይ የብድሩ ተጠቃሚ የሚሆኑ ወጣቶች እንደሆኑ ተነግሯል። ልክ የዛሬ ዓመት ህወሃት እንዲሁ በኦሮሚያ ላፈሰሰው ደም ፋብሪካ መክፈቻ 2.4 ቢሊዮን ብር ጉቦ እሰጣለሁ ብሎ ነበር። ያንን ሳያረካክብ በያዝነው ዓመት የጥቅምት ወር ላይ ደግሞ “የአስከሬን መግዣ” 10ቢሊዮን ብር እሰጣለሁ ማለቱ አይዘነጋም። ይህ ሁሉ ተስፋ የሚሰጠው ለወጣቱ ቢሆንም የዓመጽ ፍርሃቻ ሰንጎ የያዘው ህወሃት ግን እስካሁን ወጣቱና ገንዘብ እንዳይገናኙ አድርጓል፡፡

የኦሮሚያም ሆነ የአገሪቱ መሰረታዊ ጥያቄዎች በአገዛዙ መቃብር ላይ በመቆም እንጂ በኦህዲድ ቢሮ በር ላይ በሥራ አጥነት ሥም በመሰለፍ እንደማይመለስ የኦሮሞ ወጣቶች ከገባቸው ቆይቷል። የኦሮሚያ “የኢኮኖሚ አብዮት” የኦሮሞ ወጣቶች ሬሳ ላይ በመቆም በህወሃት የተደረሰ የፖለቲካ ቲያትር መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። በተለይ የድርሰቱ ዋልታና ማገር ከብአዴን መክዳት ጋር በአማራው ክልል የተነሳው ነፍጥ ያነገበ የኃይል እርምጃና “የኦሮሞና የአማራ መተባበር” ስለመሆኑ እነአባይ ጸሃዬ የመሰከሩለት ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ ከጸጥታና ደኅንነት ጋር በተገናኘ የህወሃትን የገቢ ምንጭ ክፉኛ ጎድቶታል። ስለዚህ ጉዳዩ ወደ ሁለት ግምባር ከማደጉ በፊት ሰሜን ምዕራቡን “ልክ ለማስገባት” ኦህዴድን በቅድሚያ በ“ጭድ” መደለል የግድ ነው – በህወሃት ስሌት።

ኦህዴድ በህወሃት ድርሰትና ባርኮት ወደ አደባባይ ያወጣው የኢኮኖሚ አብዮት በክልሉ አድማሱን እያሰፋ የመጣውን ድርቅ የዜና ሽፋን ለመጋረድ የጠቀመው ቢመስልም መሬት ላይ ያለው ሀቅ ግን ከዚህ የተለየ ነው። በቀጣይ ጊዜያት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ የደህንነት ስጋቶች እንደተጠበቁ ሆነዉ፤ ኦሮሚያ ክልል ላይ ያለዉ ተራዛሚ ድርቅና የወጣቶቹ የበይ ተመልካችነት እንዲሁም ለዓመታት የተከማቹ ቅሬታዎች ታክለዉበት ብረት ያካተተ ገጠርና ከተማ ያዳረሰ የሽምቅ ዉጊያ የሚጠበቅ ነው። ሃዘን ያጠቃቸው “ህወሃት የፈጸመው ግፍ በየትኛውም ዘመን የሚረሳ አይሆንም” እንዳሉት።

(ጎልጉል)

Posted by on April 1, 2017. Filed under አማርኛ/Amharic. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.