Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ዳያስፖራ ቤት ገዥዎች ሦስት ዓመት ጠብቀውም ሪል ስቴቱ በቃሉ መሠረት ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ገለጹ

– ኩባንያው በውጭ ምንዛሪ እጥረት ቤቶቹን ማጠናቀቅ እንዳልቻለ ይናገራል

በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ከ40 በላይ ዳያስፖራውያን በተለያየ ጊዜ የግዥ ውል በመፈጸም፣ ከ50 በመቶ ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ የቅድሚያ ክፍያ ከፍለው እንዳጠናቀቁ ቢገልጹም፣ በ18 ወራት ውስጥ ትረከባላችሁ የተባሉትን ቤቶች ከሦስት ዓመት በኋላም ማግኘት እንዳልቻሉ ገለጹ፡፡ ይህንኑ ጥያቄያቸውንም ለሪል ስቴት አልሚው ኩባንያ አቅርበዋል፡፡

ቅዳሜ፣ መጋቢት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ቤት ከገዙት መካከል የተወሰኑት ግንባታ እየተካሄደ በሚገኝበት መሪ ሎቄ፣ የሰንሻይን ቤቶች አካባቢ በመገናኘት ተነጋግረው ነበር፡፡ የቤቶቹ ግንባታ በተጀመረው ፍጥነት መሔድ አልቻለም ያሉት ቤት ገዥዎቹ የገዟቸውን ሌግዤሪ አፓርትመንቶች መረከብ የነበረባቸው ጊዜ ቢጓተትም የቤቶቹ ግንባታ ግን ውጫዊው ክፍል እንዲሁም መዋቅራዊ ግንባታዎች ካልሆነ በቀር የማጠናቀቂያና የገጠማ ሥራዎች ገና አልተጀመሩም፡፡ በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ እየተመላለሱ እንደሚገኙ የገለጹ ቤት ገዥዎች፣ ቤቶቻቸውን ሊረከቡ ባለመቻላቸው ምክንያት ለቤት ኪራይና ለሆቴል ወጪ እንደተዳረጉ ይናገራሉ፡፡

ዳያስፖራዎቹ ግዥ የፈጸሙባቸው ቤቶች ግንባታ ተጠናቆና ተረክበው መኖር በሚጀምሩበት ወቅት፣ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሥራ ገና ጅምር ላይ መሆኑ ቅር እንዳሰኛቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ከሪል ስቴት አልሚው ጋር በተደረገ ስብሰባ፣ የቤቶቹ ግንባታ የተጓተተው አልሚው ከተኮናተረው ተቋራጭ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነ ተገልጾላቸው፣ በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም. ግንባታውን አጠናቆ ለማስረከብ ቃል ቢገባም ቃሉን መጠበቅ ሳይችል በመቅረቱ ቤት ገዥዎቹን አስቆጥቷል፡፡

ይህ በመሆኑም ቤት ገዥዎቹ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ ዳር ዳር በማለት ላይ ሳሉ የሪል ስቴት ኩባንያው ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ይርጋለም አሰፋ ተሰብሳቢዎቹን አነጋግረዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ ይርጋለም ምላሽ ከሆነ፣ የቤቶቹ ግንባታ በጥሩ ደረጃ መሄድ ጀምሮ ድንገት የተስተጓጎለው ከተቋራጭ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ነው (እሳቸው እንደሚገልጹት በርካታ ገንዘብ በተቋራጩ ስለተወሰደባቸው ነው)፡፡ ይህ በመሆኑ ምክንያት ባለፈው ዓመት በጠሩት ስብሰባ ይህንኑ ለቤት ገዥዎቹ ገልጸው፣ የቤቶቹ ግንባታ በተባለው በመስከረም ወር እንደሚጠናቀቅ ቃል መግባታቸውን አምነው፣ ይሁንና ባልተጠበቀ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመፈጠሩ ባንኮች የምንዛሪ አቅርቦት ለሪል ስቴቱ ሊሰጡ ባለመቻላቸው ግንባታቸው መጓተቱን ገልጸዋል፡፡

ይህ ችግር በመፈጠሩ ምክንያት ከውጭ የሚገቡ የማጠናቀቂያ ግንባታ ዕቃዎችን ማስገባት እንዳልቻሉ የገለጹት ወ/ሮ ይርጋለም፣ የባኞ ቤት፣ የሴራሚክ፣ የአሉሚኒየም፣ የመስኮትና በር፣ የወለል ንጣፎችንና የመሳሰሉትን ዕቃዎች ከውጭ ለማስገባት እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው ይህን ቢሉም ቤት ገዥዎቹ ግን ‹‹በ18 ወራት ያልቃል የተባለው ቤት ይህን ያህል ጊዜ ቆይቶም አለማለቁ ሰልቸችቶናል፤›› በማለት ወቀሳቸውን ለወ/ሮ ይርጋለም አቅርበዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር እንዲህ ያለው ችግር ከውል ስምምነታቸው ውጭ ከመሆኑም ባሻገር ሌሎች ሪል ስቴቶች ተመሳሳይ ችግር ባለበት አገር ውስጥ ግንባታ እያካሄዱና እያስረከቡ በመሆኑ፣ የይርጋለም ሪል ስቴት የዶላር አጥቼ ነው ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለው ዳያስፖራዎቹ ተሟግተዋል፡፡

ቤቶቹ ከዚህ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለቤት ገዥዎቹ ሊተላለፉ እንደሚችሉ ከሪፖርተር የተጠየቁት ወ/ሮ ይርጋለም፣ የውጭ ምንዛሪ እስካልተለቀቀላቸው ድረስ በዚህ ጊዜ ውስጥ ብለው መናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ካገኙ በኋላ ምናልባት በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ቤቶቹን አጠናቀው እንደሚያስረክቡ መናገር እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

በሪል ስቴቱና በቤት ገዥዎቹ መካከል በዚህ መልኩ የተደረገው ውይይት ወደ አንድ ድምዳሜ የመጣ ሲሆን፣ ከውጭ የሚገባው የግንባታ ዕቃ በአገር ውስጥ ሊገኝ ከሚችለው ጋ የሚኖረው የዋጋ ልዩነት ተሠርቶ እንዲቀርብላቸው በጠየቁት መሠረት አልሚው ተስማምቶ የዋጋ ልዩነቱን በተመለከተ ሒሳቡን ሠርቶ ለመነጋገር ቅዳሜ ሚያዝያ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በድጋሚ ለመገናኘትና የሚበጀውን አማራጭ ለመመልከት ተስማምተዋል፡፡

ሪል ስቴት ኩባንያው ሁለት የሌግዤሪ አፓርትመንት ሕንጻዎች ውስጥ አንደኛውን ገንብቶ አጠናቋል፡፡ ከ40 ያላነሱ ቤት ገዥዎች በተጠናናቀው አፓርትመንት ሕንጻ ውስጥ የሚገኙ ቤቶችን ገዝተዋል፡፡ ከእነዚህ ባሸገር ቅሬታ ያቀረቡት ሌሎች 43 ያህል ቤት ገዥዎች የሚጠባበቋቸውን ቤቶች ጨምሮ ከ80 በላይ ቤት ገዥዎች ከይርጋለም ሪል ስቴት ጋር በመዋዋል ግዥ ፈጽመዋል፡፡ በዚህ መሠረትም ከ120 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ ለአልሚው መክፈላቸውን ቤት ገዥዎቹ ቢናገሩም፣ ወ/ሮ ይርጋለም ግን ይህ ትክክለኛ እንዳልሆነ አስተባብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሪል ስቴት ዘርፍ ተዓማኒነትን እያጣ ከመጣባቸው ምክንያቶች መካከል ጥቂት የማይባሉ አልሚዎች ከቤት ገዥዎች በቅድመ ክፍያ ሰበብ የሰበሰቡትን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይዘው የውኃ ሽታ መሆናቸው ነው፡፡ ለዚህ ተወቃሽ ሲደረግ የቆየው መንግሥት፣ እንዲህ ያሉ ከፍተኛ ገንዘብ የሚዘዋወርባቸውን ገበያዎች የሚቆጣጠር ሥርዓት ማበጀት ሳይችል በመቆየቱ ለወቀሳው መነሻ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በወጣው ሕግ መሠረት ሪል ስቴት አልሚዎች ቢያንስ መሠረት ሳያወጡ፣ የሽያጭ ማስታወቂያ ቅስሳ እንዳያካሂዱ ከልክሏል፡፡ ይህም ቢሆን ከሚጠበቀው የቁጥጥር ሥርዓትና ከቤት ገዥዎች ሥጋት አኳያ የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ ሲተች ቆይቷል፡፡

ሪፖርተር

Posted by on April 14, 2017. Filed under አማርኛ/Amharic. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.