Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የተደገሰ የጥፋት ወጥመድ ይኖር ይሆን?

በትላንትናው ዕለት አንድ የማከብረው የአማራ አክቲቪስት ወንድሜ ሚስጥራዊ መረጃ በሚል ከሃገር ቤት የተላከ ጽሁፍ አጋራኝ። ጽሁፉ የተዘጋጀው ብዙ የመንግስት ሚስጥራትን በሚያውቅ ብርቱ የፖለቲካ ታጋይ አማካኝነት እንደሆነ መገመት የሚቻል ሲሆን ስለ ፖለቲካ ዕስረኞች መፈታት ድንገተኛ ውሳኔ፤ ስለ ማዕከላዊ መዘጋት ፤ ቴዲ አፍሮ አስመራ ለምን እዘፍናለሁ እንዳለ፤ ለምንስ ባህርዳር እንደተፈቀደለት እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በምስራቅ አፍሪካ እየተካሄደ ስላለው የጦርነት ዝግጅት እና የአሜሪካ ጣልቃገብነት ሰፋ ያለ ነገር ይዟል። ጽሁፉን ካነበብኩ በኋላ እስካሁንም ድረስ አዕምሮየ በጥያቄዎች እንደተሞላ ነው (ጽሁፉን ወደበኋላ አጋራችኋለሁ ላላገኛችሁት። አሁን ግን ወደተነሳሁበት አጀንዳ ልመለስ)

ይህ ሰሞን አማራ ‘ክልልን’ በተመለከተ የሚሰሙት ዜናዎች እና ድራማዎች ልብ ብሎ በጥልቀት ለተመለከታቸው እጅጉን አስገራሚ እና ጥርጣሬ የሚጭሩ ናቸው። ለምሳሌ ሁለት ዜናዎችን እንውሰድ

★ከ4 ቀናት በፊት የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት መፈቀዱን ተወዳጁ አርቲስት ቴዲ አፍሮ እና የብአዴኑ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን በአንድ አይነት ድምጸት በደቂቃዎች ልዩነት ነገሩን። ይህ ዜና ለአርቲስቱ እና ለእኛ ለደጋፊዎች ትልቅ ዜና ከመሆኑ አንጻር በሰበር ዜና ብንቀባበለው የሚገርም አይደለም። ነገር ግን መንግስት የአንድን አርቲስት መደበኛ የኮንሰርት ስራ እንደ ትልቅ የፖለቲካ ውሳኔ የሚያወራ እና የሚያስወራ ከሆነ መሃል ላይ የታሰበ ወጥመድ ወይንም አሻጥር ስለመሆኑ በድፈረት መናገር ይቻላል።

ቴዲ አፍሮ ማለት እኮ ለባለፉት ብዙ አመታት አይደለም በብሄራዊ ስታዲየም በነጻነት ኮንሰር ማዘጋጀት ይቅርና በቤቱ እንኳ ለመቀመጥ በደህንነት ሃይሎች ወከባ ሲደርስበት የነበረ ሰው ነው። በህዋሃት ነፍሰ በላዎች ዛቻ እና ማስፈራሪያ ሲደርስበት የነበረ አርቲስት ነው። አሁን በድንገት የሃገሪቱ መንግስት ተነስቶ ለምን ፈቀደለት? ደግሞ እጅግ አስገራሚው ነገር ቴዲ አፍሮ ኮንሰርቱን ባህርዳር እንዲያቀርብ አዲስ አበባ ድረስ ሄደው የለመኑት እና ያግባቡት አቶ ንጉሱ ጥላሁን እና የአቶ ገዱ ተወካይ አቶ ምግባሩ ከበደ መሆናቸውን ነው (ከታች ያለውን የመጀመሪያውን ምስል ይመልከቱ)። ይህ በተአምር ያልተለመደ እና ጥያቄ የሚያጭር ነው።

★ሁለተኛው ዜና ደግሞ የእንጅባራ እና መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲዎች ምርቃትን የተመለከተ ነው። ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁት በሃይለማርያም ደሳለኝ፤ ደመቀ መኮነን፤ አባዱላ ገመዳ፤ ገዱ አንዳርጋቸው እና በእነ አለምነው መኮነን አማካኝነት ነው። ለመሆኑ እንደ አሸን እየበቀሉ ላሉ ዩኒቨርሲቲዎች ከመቸ ጀምሮ ነው የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር፤ ምክትሉ እና አፈጉባኤው በአንድ ላይ ሆነው ዩኒቨርሲቲ የሚመርቁት? ለምንስ አማራ ክልል ብቻ? 4ኛው ትውልድ ከሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እነ ደምቢዶሎ፤ ቦንጋ፤ ጂንካ፤ ወራቤ እና ቀብሪድሃር እንዴት እንደተመረቁ ሳንሰማ አማራ ክልል የሚገኙት እንጅባራ እና መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲዎች ግን በታላቅ ስነስርአት በሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ለዚያውም በማግስቱ ወደ ግብጽ በረራ እያለበት መመረቁን ስንሰማ የሆነ ደስ የማይል ሽታ እንዳለ እንረዳለን።

አሁን ወደ ጽሁፉ አንድ አንኳር መልዕክት ልመለስ እና ላብቃ። ጽሁፉ እንደሚለው የአሜሪካ መንግስት በምስራቅ አፍሪካ ጦርነት እንደሚነሳ እርግጠኛ ስለሆነ ኢትዮጵያ እንድትዘጋጅ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፏል። ግብጽ፤ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እና ኤርትራ በአንድ በኩል፤ ቱርክ፤ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በሌላ በኩል ለጦርነቱ እየተዘጋጁ ነው። ሱዳን ከኤርትራ ጋር ያላትን ድንበር ዘግታለች። ከሰላ ላይ ጦሯን አስፍራለች፤ ወያኔም ጦሩን ከሱዳን ጋር አስፍሯል። ከወያኔ ጋር ግንኙነት ያላቸው ጦር የጫኑ የቱርክ መርከቦች በግብጽ ታግደዋል። የአካባቢው ሰላም ደፍርሷል።

የአሜሪካ መንግስትም ይህንን የማይቀረውን ጦርነት ኢትዮጵያ በአሸናፊነት ትወጣ ዘንድ መጀመሪያ የውስጥ ችግሯን እንድትፈታ ለወያኔ ማሳሰቢያ ልኳል። እስረኞችን በመፍታት ሃገራዊ መግባባት መፍጠር፤ ለእንደ እነ ቴዲ አፍሮ አይነት የአንድነት አቀንቃኞች ስራቸውን እንዲያቀርቡ በመፍቀድ የህዝቡን ወኔ እና አንድነት ማነሳሳት እና ከመንግስት ጎን እንዲቆም ማድረግ እንደሚገባ አሜሪካ አሳስባለች ፤ ወያኔ ተግባራዊ እያደረገ ያለውም ይህንኑ ነው ይላል ጽሁፍ።

እየሆነ ያለውን ነገር በትኩረት አይተን እና መርምረን ለዚህ የጦርነት ድግስ ዋና ሞተር የአማራ ህዝብ እንዲሆን ስለተፈለገ ነው ይህ ሁሉ እሽሩሩ የሚካሄደው ብለን ብንደመድም የተሳሳትን አይመስለኝም። ከህዝቡ የጦርነት ታሪክ አኳያ፤ ከጂኦግራፊያዊ አቀማመጡ እና ከሃገሪቱ የአንድነት መንፈስ አስኳልነቱ አንጻር በውጭ ያሉት እነ አሜሪካ ሆነ የሀገር ውስጦቹ ወያኔዎች የአማራን ህዝብ ለዚህ ወጥመድ መሪ እና ዋና ተዋናይ ሊያደርጉት ቢፈልጉ የሚገርም አይሆንም…

ንስሮች ሆይ በዙሪያችን እየተካሄደ እያለውን ነገር ቆም ብለን እንመርምረው፤ ሁሉንም በትኩረት እንከታተል፤ የአማራ ደም መፍሰስ ካለበትም ለራሱ እና ለማንነቱ እንጂ ለሃገር ውስጥ ቀኝ ገዥዎች እና ለውጭ ኢምፔሪያሊስቶች ሊሆን አይችልም።

አበቃሁ!

Yohannes Amhara እንደከተበው::

#ልሣነ_ዐማራ
#AmharaPress

Posted by on January 15, 2018. Filed under News,አማርኛ/Amharic. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.